ሕዝቅኤል 1:21-27 NASV

21 ፍጡራኑ ሲንቀሳቀሱ ይን ቀሳቀሳሉ፤ ፍጡራኑ ቀጥ ብለው ሲቆሙ እነርሱም ይቆማሉ፤ ፍጡራኑ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ።

22 ከሕያዋኑ ፍጡራን ራስ በላይ የሚያስፈራና፤ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር።

23 ከጠፈሩም በታች የአንዱ ክንፍ ወደ ሌላው ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዱም ሰውነቱን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፍ ነበረው።

24 ፍጡራኑ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሰማሁ፤ ድምፁም እንደሚጐርፍ ውሃ ጩኸት፣ ሁሉን እንደሚችል አምላክ ድምፅና እንደ ሰራዊት ውካታ ነበር። መንቀሳቀሳቸውን ሲያቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25 መንቀሳቀሳቸውን አቁመው ክንፎቻቸውን ዝቅ እንዳደረጉ፣ ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ድምፅ ተሰማ።

26 ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የሰው መልክ የሚመስል ነበር።

27 ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ በእሳት መካከል እንዳለ የጋለ ብረት፣ ከወገቡም በታች እሳት ይመስል እንደነበር አየሁ፤ ደማቅ ብርሃንም በዙሪያው ነበር።