4 በቀን እያዩ ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ አውጣው፤ በምሽትም እያዩህ ስደተኛ እንደሚወጣ ውጣ።
5 እነርሱ እያዩ ግንቡን ነድለህ ጓዝህን በዚያ አሹልክ።
6 በፊታቸው ጓዝህን በትከሻህ ላይ አስቀምጥ፣ በምሽትም ተሸክመህ ውጣ። ለእስራኤል ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና ምድሪቱን እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።”
7 እኔም በታዘዝሁት መሠረት አደረግሁ፤ በቀን ጓዜን ጠቅልዬ እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፤ በምሽትም ግንቡን በእጄ ነደልሁት፤ እያዩኝም በምሽት ጓዜን በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ አወጣሁ።
8 በማግስቱም ጠዋት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
9 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ የምታደርገው ምንድን ነው?’ ብለው ጠይቀውህ አልነበረምን?”
10 “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በዚያ ለሚገኙት ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው’ ”።