1 ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።
2 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን?
4 ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ።
5 በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’
6 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ።”
7 “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ።