ሕዝቅኤል 14:2-8 NASV

2 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን?

4 ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ።

5 በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’

6 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ።”

7 “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ።

8 ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።