27 ስለዚህ ክንዴን በአንቺ ላይ አንሥቼ ድርጎሽን ቀነስሁ፤ ከክፉ መንገድሽም የተነሣ በብልግናሽ ለሚያፍሩ ጠላቶችሽ ለፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አሳልፌ ሰጠሁሽ።
28 ገና ስላልረካሽም ከአሦራውያን ጋር ደግሞ አመነዘርሽ፤ ከዚያም በኋላ እንኳ አልረካሽም።
29 ርኵሰትሽንም እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ባቢሎን ድረስ አበዛሽ፤ ያም ሆኖ አልረካሽም።
30 “ ‘እንደ ዐይን አውጣ አመንዝራ ይህን ሁሉ መፈጸምሽ ምን ዐይነት ደካማ ልብ ቢኖርሽ ነው! ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31 በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይ ጒብታሽን ባበጀሽና በየአደባባዩም መስገጃ ኰረብታ በሠራሽ ጊዜ እንደ ማንኛውም ዝሙት አዳሪ አልነበርሽም፤ ምክንያቱም ዋጋ አላስከፈልሽም።
32 “ ‘አንቺ ከገዛ ባሏ ይልቅ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ነሽ!
33 ማንኛዋም አመንዝራ ሴት ዋጋ ይከፈላታል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ስጦታ ታበረክቻለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ እጅ መንሻ ታቀርቢላቸዋለሽ።