ሕዝቅኤል 16:48-54 NASV

48 እኔ ሕያው እግዚአብሔር! በራሴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴት ልጆችሽ ያደረጋችሁትን እኅትሽ ሰዶምና ልጆቿ እንኳ አላደረጉትም።

49 “ ‘እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር።

50 ኵራተኞች ነበሩ፤ በፊቴ አስጸያፊ ተግባር መፈጸማቸውን ባየሁ ጊዜም አስወገድኋቸው።

51 ሰማርያ አንቺ ያደረግሽውን ኀጢአት ግማሹን እንኳ አልሠራችም። አንቺ ግን ከእነርሱ የባሰ አስጸያፊ ተግባር በመፈጸምሽ፣ በዚህ ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው።

52 እኅቶችሽን እንደ ጻድቃን በማስቈ ጠርሽ፣ ዕፍረትሽን ተከናነቢ፤ ኀጢአትሽ ከኀጢአታቸው የከፋ ስለ ሆነ፣ እነርሱ ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ሆኑ። እንግዲህ እኅቶችሽን ጻድቃን ስላስመሰልሻቸው፣ አንቺ ተዋረጂ፤ ዕፍረትሽንም ተከናነቢ።

53 “ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ።

54 ይህም የሚሆነው ለእነርሱ መጽናኛ በመሆንሽ እንድ ትዋረጂና ባደረግሽው ሁሉ እንድታፍሪ ነው።