ሕዝቅኤል 17:13-19 NASV

13 ከንጉሣውያን ቤተ ሰብ አንዱን ወስዶ ከእርሱ ጋር ውል አደረገ፤ በመሐላም ቃል አስገባው፤ የምድሪቱንም ታላላቅ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤

14 ይኸውም የምድሪቱ መንግሥት ተዋርዳ የእርሱን ውል በመጠበቅ ብቻ እንድትኖር እንጂ፣ ዳግመኛ እንዳታንሰራራ ለማድረግ ነበር።

15 ንጉሡ ግን በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ ፈረሶችና ብዙ ሰራዊት ለማግኘት መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ላከ፤ ይሳካለት ይሆን? እንዲህ ዐይነቱን ነገር የፈጸመ ያመልጣልን? ውል ያፈረሰስ ሳይቀጣ ይቀራልን?

16 “ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ መሐላውን ባቀለለበት፣ ውሉን ባፈረሰበት፣ በዙፋንም ላይ ባስቀመጠው ንጉሥ ምድር በባቢሎን ይሞታል።

17 በባቢሎናውያን ብዙ ሕይወት ለማጥፋት በከተማዋ ዙሪያ ዐፈር በሚደለድሉበትና ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፣ ፈርዖን ከኀያል ሰራዊቱና ከብዙ ጭፍሮቹ ጋር በጦርነት ሊረዳው አይችልም።

18 ያደረገውን መሐላ በማቃለልና እጁን ያስገባበትን ውል በማፍረስ ይህን ሁሉ ስለ ፈጸመ ከቅጣት አያመልጥም።

19 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ ያቃለለውን መሐላዬንና ያፈረሰውን ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።