ሕዝቅኤል 18:14-20 NASV

14 “ይህም ልጅ ደግሞ በተራው ልጅ ቢወልድና ልጁም አባቱ ያደረገውን ኀጢአት ሁሉ አይቶ ባይፈጽም፣ ይኸውም፦

15 በኰረብታ መስገጃ የቀረበውን ባይበላ፣በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት ባይመለከት፣የባልንጀራውን ሚስት ባያባልግ፣

16 ሰውን ባይጨቍን፣ብድር ለመስጠት መያዣ ባይጠይቅ፣በጒልበቱ ባይቀማ፣ነገር ግን ምግቡን ለተራበ፣ልብሱን ለተራቈተ ቢሰጥ፣

17 እጁን ደኻን ከመበደል ቢሰበስብ፣ዐራጣ ወይም ከፍተኛ ወለድ ባይቀበል፣ሕጌን ቢጠብቅ፣ ሥርዐቴንም ቢከተል፣በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኀጢአት አይሞትም።

18 አባቱ ግን የሰውን መብት ስለደፈረ፣ ወንድሙን በጒልበት ስለ ቀማና በሕዝቡ መካከል የማይገባውን ስላደረገ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል።

19 “እናንተ ግን፣ ‘ልጅ ስለ አባቱ ኀጢአት ለምን አይቀጣም?’ ትላላችሁ። ልጁ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ስላደረገ፣ ሥርዐቴንም ሁሉ በጥንቃቄ ስለ ጠበቀ በሕይወት ይኖራል።

20 መሞት የሚገባት ኀጢአት የሠራችው ነፍስ ናት። ልጅ በአባቱ ኀጢአት አይቀጣም፤ አባትም በልጁ ኀጢአት አይቀጣም። ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል፤ ኀጢአተኛውም የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።