ሕዝቅኤል 18:21-27 NASV

21 “ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ ተመልሶ ሥርዐቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።

22 በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፤ በጽድቅ መንገድ ሄዶአልና በሕይወት ይኖራል።

23 በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?

24 “ጻድቅ ሰው ግን ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ ኀጢአተኛው የሚያደርገውንም አስጸያፊ ነገር ቢፈጽም፤ ይህ ሰው በውኑ በሕይወት ይኖራልን? ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና ከፈጸመው ኀጢአት የተነሣ ይሞታል።

25 “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን?

26 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም።

27 ኀጢአተኛው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ በታማኝነትና በቅንነት ቢኖር ሕይወቱን ያድናል።