40 በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋር በዚያ እሻለሁ።
41 ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበ ሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
42 ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
43 በዚያም መንገዳችሁንና ራሳችሁን ያረከሳችሁበትን ተግባር ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በፈጸማችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
44 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ብልሹ ተግባራችሁ ሳይሆን፣ ስለ ስሜ ስል በምጐበኛችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
45 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
46 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ደቡብ አዙር፤ በደቡብ ላይ ቃል ተናገር፤ በደቡብ አገር ደን ላይም ትንቢት ተንብይ።