ሕዝቅኤል 25:2-8 NASV

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ አሞናውያን አድርገህ፣ ትንቢት ተናገርባቸው፤

3 እንዲህም በላቸው፤ ‘የጌታ፣ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፣ የይሁዳም ቤት ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ፣ ‘እሰይ’ ብላችኋልና፣

4 ለምሥራቅ ሕዝብ ትገዙ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በመካከላችሁ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውንም በዚያ ይተክላሉ፤ ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።

5 የራባን ከተማ የግመሎች መሰማሪያ፣ አሞንንም የበጎች መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

6 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በልባችሁ ክፋት ሁሉ፣ በእስራኤል ውድቀት ላይ በመደሰት በእጃችሁ አጨብጭባችኋልና፤ በመዝለልም ጨፍራችኋልና

7 ክንዴን በእናንተ ላይ አነሣለሁ፤ በአሕዛብ እንድትበዘበዙ አደርጋለሁ፤ ከሕዝቦች መካከል አውጥቼ፣ ከአገሮችም ለይቼ አጠፋችኋለሁ፤ እደመስሳችኋለሁም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

8 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሞዓብና ሴይር፣ “እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎቹ አሕዛብ ሁሉ ሆነ” ብለዋልና፤