1 በዐሥረኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን አዙር፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤
3 እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።“ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ።“የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።
4 ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋር፣ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ።