10 ስለዚህ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በወንዞችህ ላይ ተነሥቻለሁ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል እስከ አስዋን ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ።
11 የሰው እግርም ሆነ የእንስሳ ኮቴ በውስጧ አያልፍም፤ እስከ አርባ ዓመት ማንም አይኖርባትም።
12 የግብፅን ምድር ከጠፉት ምድሮች መካከል እንደ አንዱ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከተሞቿም በፈራረሱት ከተሞች መካከል አርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።
13 “ ‘ያም ሆኖ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑበት አገሮች መካከል እሰበስባቸዋለሁ።
14 ከተማረኩበት አመጣቸዋለሁ፤ ወደ አባቶቻቸው ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ።
15 ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች፤ ከሌሎችም አሕዛብ በላይ ራሷን ከፍ ማድረግ አትችልም። እጅግ ደካማ አደርጋታለሁ፤ ስለዚህ ሌሎችን አሕዛብ እንደ ገና መግዛት አትችልም።
16 ግብፅ ከእንግዲህ ለእስራኤል ሕዝብ መታመኛ አትሆንም፤ ለርዳታ ወደ እርሷ ዘወር ባሉ ጊዜ ላደረጉት ኀጢአት ግን መታሰቢያ ትሆናለች። ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”