ሕዝቅኤል 30:20-26 NASV

20 በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ ይፈወስ ዘንድ ክንዱ አልተጠገነም፤ ወይም ሰይፍ መያዝ ይችል ዘንድ እጁ በመቃ አልታሰረም።

22 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነሥቻለሁ፤ ደኅናውንና የተሰበረውን፣ ሁለቱንም ክንዶቹን እሰብራለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።

23 ግብፃውያንን በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

24 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ ሰይፌንም አስይዘዋለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፤ እርሱም በፊቱ ክፉኛ እንደ ቈሰለ ሰው ያቃስታል።

25 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ ሳስይዝ፣ እርሱም ሲነቀንቀው፣ ያኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።

26 በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”