ሕዝቅኤል 32:12-18 NASV

12 ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ ጨካኝ በሆኑት፣በኀያላን ሰዎች ሰይፍ፣ያከማቸኸው ሰራዊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤የግብፅን ኵራት ያንኰታኵታሉ፤የሰራዊቷም ብዛት ይጠፋል፤

13 ብዙ ውሃ ባለበት አጠገብ ያለውን፣የከብት መንጋዋን አጠፋለሁ፤ከእንግዲህ የሰው እግር አይረጋግጠውም፤የከብትም ኮቴ አያደፈርሰውም።

14 ከዚያም ውሆቿን አጠራለሁ፤ወንዞቿም እንደ ዘይት እንዲፈሱ አደርጋለሁ፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15 ግብፅን ባድማ ሳደርጋት፣ምድሪቱም ያላትን ሁሉ ያጣች ስትሆን፣በዚያም የሚኖሩትን ሁሉ ስመታ፣ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

16 “ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብፅና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

17 በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብፅ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው።