ሕዝቅኤል 33:23-29 NASV

23 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በእርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ።

25 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ?

26 በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’

27 “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ።

28 ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጒልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ።

29 ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’