ሕዝቅኤል 33:5-11 NASV

5 የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር።

6 ነገር ግን ጒበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጒበኛውን ግን ስለ ሰውዬው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’

7 “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጒበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው።

8 ክፉውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።

9 ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።

10 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘እንዲህ ትላላችሁ፤ “በደላችንና ኀጢአታችን ከብዶናል፤ ከዚህም የተነሣ ልንጠፋ ነው፤ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን?’

11 እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’