ሕዝቅኤል 34:2-8 NASV

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ራሳቸውን ብቻ ለሚንከባከቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች መንጋውን ማሰማራት አልነበረባቸውምን?

3 ጮማውን ትበላላችሁ፤ ከጠጒሩ የተሠራውን ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውን ዐረዳችሁ፤ ነገር ግን መንጋውን አትንከባ ከቡትም።

4 ደካማውን አላበረታችሁትም፤ በሽተኛውን አልፈወሳችሁትም፤ የተጐዳውንም አልጠገናችሁትም። የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትንም አልፈለጋችሁም፤ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው።

5 ስለዚህ እረኛ የለምና ተበተኑ፤ በመበተናቸውም ለአራዊቱ ሁሉ መብል ሆኑ።

6 በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኰረብታው ላይ ተንከራተቱ። በምድር ሁሉ ተበተኑ፤ የፈለጋቸውም፤ የፈቀዳቸውም የለም።

7 “ ‘ስለዚህ እናንት እረኞች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

8 በሕያውነቴ እምላለሁ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኞቼ መንጋዬን ስላልፈለጉ፣ ከመንጋዬም ይልቅ ራሳቸውን ስለተንከባከቡ፣ መንጋዬ እረኛ አጥቶ ለንጥቂያ ተዳርጎአል፤ ለአራዊትም ሁሉ መብል ሆኖአል።