ሕዝቅኤል 37:1-7 NASV

1 የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም በእግዚአብሔር መንፈስ አወጣኝ፤ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ ሸለቆውም በዐጥንቶች ተሞልቶ ነበር።

2 በእነርሱም መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ አመላለሰኝ፤ በሸለቆውም ወለል ላይ በጣም የደረቁ እጅግ ብዙ ዐጥንቶች አየሁ።

3 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” ሲል ጠየቀኝ።እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ብቻ ታውቃለህ” አልሁ።

4 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!

5 ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ “እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ።

6 ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቆዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’

7 ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽ ኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ።