ሕዝቅኤል

ምዕራፎች 37:6-12

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

6ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቆዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’ 7ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽ ኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ። 8እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቆዳም ሸፍኖአቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። 9ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።” ’ 10ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። 11ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።” 12ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።