7 ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽ ኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ።
8 እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቆዳም ሸፍኖአቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።
9 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።” ’
10 ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።”
12 ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።
13 ከዚያም እናንተ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን ከፍቼ ሳወጣችሁ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።