ሕዝቅኤል 4:3-9 NASV

3 የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።

4 “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቊጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ።

5 እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቊጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።

6 “ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ።

7 ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት።

8 የከበባህን ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጐን ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ።

9 “ስንዴና ገብስ፣ ባቄላና ምስር እንዲሁም ዘንጋዳና ጠመዥ ወስደህ በአንድ ሸክላ ውስጥ አስቀምጥ፤ ከዚያም ለራስህ እንጀራ ጋግር፤ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን በጐንህ በምትተኛበት ጊዜ ትመገበዋለህ።