ሕዝቅኤል
ምዕራፎች 43:18-24
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
18ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤”
19በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20ከደሙም ጥቂት ወስደህ፣ በመሠዊያው አራት ቀንዶች፣ በላይኛው ዕርከን አራት ጐኖች ላይ እንዲሁም በጠርዙ ዙሪያ ሁሉ ታደርጋለህ፤ በዚህ ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻለህ፤ ታስተሰርይለታለህም።
21ወይፈኑን ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወስደህ፣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ከመቅደሱ ውጩ ለዚሁ ተብሎ በተመደበው ስፍራ ታቃጥለዋለህ።
22“በሁለተኛው ቀን እንከን የሌለበት ተባት ፍየል ወስደህ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለህ፤ መሠዊያው በወይፈኑ እንደ ነጻ ሁሉ፣ በዚህም መንጻት አለበት።
23ማንጻቱን ከፈጸምህ በኋላ፣ ከመንጋው እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ ታቀርባለህ።
24በእግዚአብሔር ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱ ጨው ይነሰንሱባቸዋል፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቧቸዋል።