ሕዝቅኤል 44:25-31 NASV

25 ‘ “ካህን ወደ ሞተ ሰው ሬሳ በመጠጋት ራሱን አያርክስ፤ ይሁን እንጂ ሟች አባቱ ወይም እናቱ፣ ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ፣ ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ብትሆን፣ ራሱን ማርከስ ይችላል።

26 ከነጻም በኋላ፣ ሰባት ቀን መቈየት አለበት።

27 በመቅደሱ ለማገልገል፣ ወደ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ቀን፣ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

28 ‘ “ለካህናቱ ርስታቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ በእስራኤል ምንም ዐይነት ርስት አትስጧቸው፤ እኔ ርስታቸው እሆናለሁ።

29 የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕትይበላሉ፤ በእስራኤል ለእግዚአብሔር የተሰጠው ሁሉ የእነርሱ ይሆናል።

30 ከፍሬ በኵራት ምርጥ የሆነው ሁሉ እንዲሁም ከልዩ ስጦታዎቻችሁ የመጀመሪያው ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ ለቤተ ሰዎቻችሁ ሁሉ በረከት እንዲሆን ከምድር የምታገኙትን መብል በኵራት ለእነርሱ ስጧቸው።

31 ካህናት ሞቶ የተገኘውን ወይም በዱር አራዊት የተዘነጠለውን ወፍም ይሁን ሌላ እንስሳ፣ ማንኛውንም ነገር መብላት የለባቸውም።