ሕዝቅኤል 45:8-14 NASV

8 ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዡ ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዦቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል።

9 ‘ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

10 ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ።

11 የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው።

12 አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ አምስት ሰቅልና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል።’

13 ‘ “የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆመር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆመር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው።

14 ዘይቱ በባዶስ ሲለካ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆመር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆመር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆመር ጋር እኩል ነውና።