ሕዝቅኤል 46:1-7 NASV

1 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ለምሥራቅ ትይዩ የሆነው የውስጠኛው አደባባይ በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ይዘጋ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በወር መባቻ ቀን ይከፈት።

2 ገዡ ከውጭ በኩል በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ በመግባት በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፤ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ በበሩ መግቢያ ደፍ ላይ ሆኖ ይስገድ፤ ከዚያም ይውጣ፤ በሩ ግን እስከ ምሽት ድረስ አይዘጋ።

3 የምድሪቱም ሕዝብ በሰንበታትና በወር መባቻ በዓላት በእግዚአብሔር ፊት በበሩ መግቢያ ላይ ይስገዱ።

4 ገዡ በሰንበት ቀን በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ነው፤ ሁሉም እንከን የሌላቸው ይሁኑ።

5 ከአውራ በጉ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበውም የእህል ቍርባን ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።

6 በወር መባቻ በዓል አንድ ወይፈን፣ ስድስት የበግ ጠቦትና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ።

7 ከወይፈኑ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ከአውራው በግም ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ከበግ ጠቦቶቹ ጋር የሚቀርበው የእህል ቍርባን ደግሞ ሰውየው የወደደውን ያህል ይሁን፤ እያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይኑረው።