1 ከዚያም ያ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መልሶ አመጣኝ፤ ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ እየወጣ፣ ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ለምሥራቅ ትይዩ ነበርና። ውሃው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል፣ በመሠዊያው ደቡብ በኩል፣ ሥር ሥሩን ይወርዳል።
2 ከዚያም በሰሜኑ በር በማውጣት በውጭ አዙሮ በምሥራቅ አቅጣጫ ወዳለው የውጭ በር መራኝ፤ ውሃውም በደቡብ በኩል ይፈስ ነበር።
3 ያም ሰው የመለኪያውን ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ በመሄድ፣ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ ከዚያም እስከ ቁርጭምጭሚት በሚደርሰው ውሃ ውስጥ መራኝ፤
4 ቀጥሎም አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ እስከ ጒልበት ወደሚደርስም ውሃ መራኝ፤ ከዚያም ሌላ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ እስከ ወገብ ወደሚደርስም ውሃ መራኝ።
5 እንደ ገናም አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ አሁን ግን ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ ምክንያቱም ውሃው ስለ ሞላና ጥልቅ ስለ ነበረ፣ በዋና ካልሆነ በስተቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ነበረ።
6 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ታየዋለህን?” ሲል ጠየቀኝ።ከዚያም መልሶ ወደ ወንዙ ዳር መራኝ፤
7 እዚያም በደረስሁ ጊዜ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ብዙ ዛፍ አየሁ።