ሕዝቅኤል 9:6-11 NASV

6 ሽማግሌውን፣ ጒልማሳውንና ልጃገረዲቱን፤ ሴቶችንና ሕፃናትን ፈጽማችሁ አጥፉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ያለበትን ሰው አትንኩ፤ ከቤተ መቅደሴም ጀምሩ።” ስለዚህ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ከነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ።

7 እርሱም፣ “ቤተ መቅደሴን አርክሱ፤ አደባባዩንም ሬሳ በሬሳ አድርጉ፤ ሂዱ!” አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማዪቱ ሁሉ እየተዘዋወሩ መግደል ጀመሩ።

8 እነርሱ እየገደሉ እኔም ብቻዬን ሳለሁ፣ በግንባሬ ተደፍቼ፣ “ወዮ! ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ በኢየሩሳሌም ላይ መዓትህን አውርደህ የእስራኤልን ትሩፋን ሁሉ ልታጠፋ ነውን?” በማለት ጮኽሁ።

9 እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፤ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኀጢአት እጅግ በዝቶአል፤ ምድሪቱ በደም ተጥለቅልቃለች፤ ከተማዪቱም ግፍን ተሞልታለች። እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል፤ እግዚአብሔር አያይም’ ይላሉ፤

10 እኔም የሠሩትን ሥራ በራሳቸው ላይ እመልስባቸዋለሁ እንጂ በርኅራኄ ዐይን አላያቸውም፤ ከሚመጣባቸውም ነገር አላድናቸውም።”

11 እነሆ በፍታ የለበሰውና በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበው ሰው ተመልሶ፣ “እንዳዘዝኸው ፈጽሜአለሁ” አለ።