ኢሳይያስ 16:6-12 NASV

6 የሞዓብን መዘባነን፣እጅግ መታበዩንና ኵራቱን፣እብሪቱንና ስድነቱን ሰምተናል፤ትምክህቱ ግን ከንቱ ነው።

7 ስለዚህ ሞዓባውያን ዋይ ይላሉ፤በአንድነትም ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማሉ፤ስለ ቂርሐራሴት ከተማ ሰዎች ትዝታ፣በሐዘን ያለቅሳሉ።

8 የሐሴቦን ዕርሻ፣የሴባማም የወይን ተክል ጠውልጎአል፤የአሕዛብ ገዦች፣ኢያዜርን ዐልፈው፣ምድረ በዳውን ዘልቀው፣ሥሮቻቸውን እስከ ባሕር ሰድደው የነበሩትንየተመረጡ የወይን ተክሎችንረጋግጠዋል።

9 ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ተክል፣ኢያዜር እንዳለቀሰች፣ እኔም አለቅሳለሁ፤ሐሴቦን ሆይ፤ ኤልያሊ ሆይ፤በእንባዬ አርስሻለሁ፤ፍሬ ባፈራሽበት ወቅት የነበረው ሆታ፣መከርሽም ሲደርስ የነበረው ደስታ ተቋርጦአልና።

10 ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤እልልታም ቀርቶአል።በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና።

11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጒርጒሮ ታሰማለች፤አንጀቴም ስለ ቄርሔሬስ ታለቅሳለች፤

12 ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣ዋጋ የለውም።