ኤርምያስ 11:2-8 NASV

2 “የዚህን ኪዳን ቃል ስማ፤ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሰዎች ንገራቸው፤

3 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፤ ‘ለዚህ ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ይሁን፤

4 ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤

5 ዛሬም እንደሆነው ሁሉ ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የገባሁትን መሐላ እፈጽማለሁ።’ ”እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሜን” ብዬ መለስሁ።

6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የዚህን ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም፤

7 የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ “ታዘዙኝ” በማለት ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው።

8 እነርሱ ግን የክፉ ልባቸውን እልከኝነት ተከተሉ እንጂ አልታዘዙኝም፤ ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም፤ ስለዚህ እንዲከተሉት አዝዤአቸው ያላደረጉትን የዚህን ኪዳን ርግማን ሁሉ አመጣሁባቸው።’ ”