ኤርምያስ 12:10-16 NASV

10 ብዙ እረኞች የወይን ቦታዬን ያጠፋሉ፤ይዞታዬንም ይረግጣሉ፤ደስ የምሰኝበትንም ማሳ፣ጭር ያለ በረሓ ያደርጉታል።

11 በፊቴ ባድማ፣ደረቅና ወና ይሆናል፤መላዪቱም ምድር ጠፍ ትሆናለች፤ስለ እርሷ የሚገደው የለምና።

12 በምድረ በዳ ባሉት ወና ኰረብቶች ላይ፣አጥፊዎች ይሰማራሉ፤ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ፣አንዳች ሳያስቀር ይበላል፤የሚተርፍም የለም።

13 ስንዴን ይዘራሉ፤ እሾኽን ያጭዳሉ፤ይደክማሉ፤ የሚያገኙት ግን የለም፤ ከእግዚአብሔርም ጽኑ ቍጣ የተነሣ፣በመኸራችሁ ውጤት ታፍራላችሁ።”

14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሕዝቤ ለእስራኤል የሰጠሁትን ርስት የሚይዙትን ክፉ ጎረቤቶቼን ሁሉ፣ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅላለሁ፤

15 ከነቀልኋቸው በኋላ ግን መልሼ እምራቸዋለሁ፤ እያንዳንዳቸውንም ወደ ገዛ አገራቸውና ወደ ገዛ ርስታቸው መልሼ አመጣቸዋለሁ፤

16 የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩና ሕዝቤን በበኣል እንዲምል እንዳስ ተማሩት ሁሉ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው በስሜ ቢምሉ፣ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ፤