ኤርምያስ 14:10-16 NASV

10 እግዚአብሔር ስለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፤“መቅበዝበዝ እጅግ ይወዳሉ፤እግሮቻቸው አይገቱም፤ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤አሁን በደላቸውን ያስባል፤በኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።”

11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ለዚህ ሕዝብ በጎነት አትጸልይ፤

12 ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።”

13 እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ!፣ ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ።

14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።

15 ስለዚህ በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሳልልካቸው፣ ‘ሰይፍና ራብ በዚች ምድር ላይ አይመጣም’ የሚሉ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤

16 ትንቢቱ የተነገረለትም ሕዝብ ከሰይፍና ከራብ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይወድቃል፤ እነርሱንም ሆነ ሚስቶቻቸውን ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይገኝም። ለበደላቸው የሚገባውንም ቅጣት በላያቸው አወርዳለሁ።