ኤርምያስ 16:12-18 NASV

12 እናንተም ደግሞ ከአባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ እያንዳንዳችሁ እኔን በመታዘዝ ፈንታ የልባችሁን ክፋት ምን ያህል በእልኸኝነት እንደምትከተሉ ተመልከቱ።

13 ስለዚህ ከዚህች ምድር አውጥቼ፣ እናንተም ሆነ አባቶቻችሁ ወደማታውቁት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።’

14 “ስለዚህ ሰዎች፦ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

15 “ነገር ግን፣ እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ይላሉ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁና።

16 “አሁን ግን ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እነርሱም ያጠም ዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰዳለሁ፤ እነርሱም ከየተራራው፣ ከየኰረብታው ሁሉ ከየዐለቱም ስንጣቂ አድነው ይይዟቸዋል።

17 ዐይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፤ በፊቴ የተገለጡ ናቸው፤ ኀጢአታቸውም ከዐይኔ የተሰወረ አይደለም።

18 ምድሬን በድን በሆኑ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸው ስላረከሱ፣ ርስቴንም በአሳፋሪ ነገሮች ስለሞሉ፣ ላደረጉት በደልና ኀጢአት ዕጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”