1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ የመልክያን ልጅ ጳስኮርን እንዲሁም የመዕሤያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እርሱ በላከ ጊዜ፣ ቃል ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ መጣ፤ የተላኩትም እንዲህ ብለውት ነበር፤
2 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሊወጋን ስለ ሆነ፣ እባክህን ፈጥነህ፣ እግዚአብሔርን ጠይቅልን፤ ምናልባት ንጉሡ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ቀድሞው ታምራት ያደርግልን ይሆናል” ብለው ነበር።
3 ኤርምያስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ለሴዴቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤
4 ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከቅጥሩ ውጭ የከበቧችሁን የባቢሎንን ንጉሥና ባቢሎናውያንን ለመውጋት በእጃችሁ የያዛችሁትን የጦር መሣሪያ በእናንተው ላይ አዞራለሁ፤ ወደዚህችም ከተማ ሰብስቤ አስገባቸዋለሁ።