1 “በማሰማሪያ ቦታዬ ያሉትን በጎቼን ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር።
2 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፤ “መንጋዬን ስለ በተናችሁ፣ ስላባረራችሁና ተገቢውን ጥንቃቄ ስላላደረጋችሁላቸው፣ ለክፋታችሁ ተገቢውን ቅጣት አመጣባችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤
3 “የመንጋዬንም ቅሬታ ካባረርሁባቸው አገሮች ሁሉ እኔ ራሴ ሰብስቤ፣ ወደ መሰማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ይበዛሉም።
4 የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አይፈሩም፤ አይደነግጡም ከእነርሱም አንድ እንኳ አይጐድልም” ይላል እግዚአብሔር።
5 “እነሆ፤ ለዳዊት፣ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።