ኤርምያስ 23:11-17 NASV

11 “ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።”ይላል እግዚአብሔር።

12 “ስለዚህ መንገዳቸው ድጥ ይሆናል፤ወደ ጨለማ ይጣላሉ፤ተፍገምግመውም ይወድቃሉ፤በሚቀጡበትም ዓመት፣መዓት አመጣባቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

13 “በሰማርያ ባሉ ነቢያት ላይ፣ደስ የማያሰኝ ነገር አይቻለሁ፤በበኣል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ሕዝቤን እስራኤልን አሳቱ።

14 በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።”

15 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ነቢያት እንዲህ ይላል፤“ከኢየሩሳሌም ነቢያት፣በምድሪቱ ሁሉ ርኵሰት ተሠራጭቶአልና፤መራራ ምግብ አበላቸዋለሁ፤የተመረዘም ውሃ አጠጣቸዋለሁ።”

16 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።

17 እኔን ለሚንቁኝ፣‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።