10 የደስታንና የእልልታን ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን አስቀራለሁ።
11 አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።
12 “ነገር ግን ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ፤
13 በምድሪቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ ይኸውም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኤርምያስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገረውን ትንቢት አመጣባታለሁ።
14 ሕዝቧም ለብዙ ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት ባሮች ይሆናሉ፤ እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸውም ሥራ እከፍላቸዋለሁ።”
15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “በቍጣዬ የወይን ጠጅ የተሞላውን ይህን ጽዋ ከእጄ ውሰድ፤ እኔ ወደ ምልክህም ሕዝቦች ሁሉ ሄደህ አጠጣቸው።
16 በጠጡም ጊዜ ይንገዳገዳሉ፤ በመካከላቸው ከምሰደው ሰይፍ የተነሣ ያብዳሉ።”