7 ኤርምያስ ይህን ቃል በእግዚአብሔር ቤት ሲናገር፣ ካህናቱና ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ።
8 ነገር ግን ኤርምያስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ያዘዘውን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ ይዘውት እንዲህ አሉ፤ “አንተ መገደል አለብህ!
9 ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህቺም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ በእግዚአብሔር ስም ለምን ትንቢት ትናገራለህ?” ’ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተሰብስበው ኤርምያስን ከበቡት።
10 የይሁዳም ባለ ሥልጣኖች ስለ እነዚህ ነገሮች በሰሙ ጊዜ፣ ከቤተ መንግሥት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔር ቤት፣ ‘አዲሱ በር በተባለው መግቢያ ተቀመጡ።
11 ካህናቱና ነቢያቱም ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ፣ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁት ይህ ሰው በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ስለ ተናገረ ሞት ይገባዋል” አሉ።
12 ኤርምያስም፣ ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የሰማችሁትን ሁሉ በዚህ ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር እግዚአብሔር ልኮኛል።
13 አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል።