ኤርምያስ 29:4-10 NASV

4 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤

5 “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤

6 አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ።

7 ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።”

8 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤

9 በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር።

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።