ኤርምያስ 31:6-12 NASV

6 ጠባቂዎች፣ በኤፍሬም ኰረብቶች ላይ፣‘ኑ፤ ወደ ጽዮን፣ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ!’ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል።

7 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ፤ስለ ሕዝቦች አለቃ እልል በሉ፤ምስጋናችሁን አሰሙ፤‘እግዚአብሔር ሆይ፤ የእስራኤልን ቅሬታ፣ሕዝብህን አድን’ በሉ።

8 እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤በመካከላቸውም ዕውሮችና አንካሶች፣ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።

9 እያለቀሱ ይመጣሉ፤እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣በውሃ ምንጭ ዳር፣በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።

10 “ሕዝቦች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ።

11 እግዚአብሔር ያዕቆብን ይዋጀዋልና፤ከእርሱም ከሚበረቱት እጅ ይታደገዋልና።

12 መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ከእንግዲህም አያዝኑም።