ኤርምያስ 38:6-12 NASV

6 ስለዚህ ኤርምያስን ወስደው፣ በዘበኞች አደባባይ በነበረው በንጉሡ ልጅ በመልክያ የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በገመድም ኤርምያስን ወደ ጒድጓዱ አወረዱት። ጒድጓዱም ጭቃ እንጂ ውሃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ዘልቆ ገባ።

7 በቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አቤሜሌክ፣ ኤርምያስን በውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ሳለ፣

8 አቤሜሌክ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፤

9 “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ክፋትን አድርገዋል፤ ከከተማዪቱም እንጀራ በጠፋ ጊዜ በራብ እንዲሞት ጒድጓድ ውስጥ ጥለውታል።”

10 ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፣ “ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ይዘህ ሂድ፤ ነቢዩ ኤርምያስንም ሳይሞት ከጒድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው።

11 አቤሜሌክም ሰዎቹን ይዞ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሥር ወዳለው ክፍል ሄደ፤ ያረጀ ጨርቅና ያለቀ ልብስ ከዚያ ወስዶ ወደ ኤርምያስ ወደ ጒድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደለት።

12 ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን፣ “ይህን ያረጀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ ገመዱ እንዳይከረክርህ በብብትህ ሥር አድርገው አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ፤