ኤርምያስ 43:4-10 NASV

4 ስለዚህ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና፣ የጦር መኰንኖቹ ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡ በሙሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ምድር እንዲቀመጡ ያዘዛቸውን ቃል አልሰሙም።

5 ነገር ግን፣ የቃሪያ ልጅ ዮሐናንና የጦር መኮንኖቹ ሁሉ፣ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተበተኑበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል የተመለሱትን የይሁዳን ቅሬታዎች ሁሉ ይዘው ሄዱ፤

6 በተጨማሪም ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንዲሁም የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን በአኪቃም ልጅ በጎዶልያስ እጅ የተዋቸውን የንጉሡን ሴቶች ልጆች፣ ነቢዩ ኤርምያስንና የኔርያን ልጅ ባሮክን ወሰዷቸው፤

7 የእግዚአብሔርንም ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብፅ ገቡ፤ ዘልቀውም እስከ ጣፍናስ ድረስ ሄዱ።

8 በጣፍናስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

9 “ትልልቅ ድንጋዮች ውሰድና በጣፍናስ ባለው የፈርዖን ቤተ መንግሥት በር ላይ የይሁዳ ሰዎች እያዩ በሸክላ ጡብ ወለል ውስጥ ቅበራቸው፤

10 እንዲህም በላቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አገልጋዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ዙፋኑንም እዚህ በቀበርኋቸው ድንጋዮች ላይ እዘረጋለሁ፤ የንጉሥ ድንኳኑንም በላያቸው ይተክላል።