ኤርምያስ 49:1-5 NASV

1 ስለ አሞናውያን፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እስራኤል ወንዶች ልጆች አልወለደምን?ወራሾችስ የሉትምን?ታዲያ፣ ሚልኮምሸ ጋድን ለምን ወረሰ?የእርሱ ሰዎች ለምን በከተሞቿ ይኖራሉ?

2 ስለዚህ በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ፣የጦርነት ውካታ ድምፅ፣የሚሰማበት ጊዜ ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር፤“እርሷም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤በዙሪያዋ ያሉት መንደሮችም ይቃጠላሉ፤እስራኤልም ከአገሯ ያስወጧትን፣ከአገሯ ታስወጣለች፤”ይላል እግዚአብሔር፤

3 ሐሴቦን ሆይ፤ ጋይ ጠፍታለችና ዋይ በይ፤የራባት ሴቶች ልጆች ሆይ ጩኹ፤ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤ሚልኮም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣ተማርኮ ይወሰዳልና፣በቅጥር ውስጥ ወዲያ ወዲህ ተሯሯጡ።

4 አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፣በሸለቆችሽ ለምን ትመኪያለሽ?ለምንስ በፍሬያማ ሸለቆሽ ትኵራሪያለሽ?በብልጽግናሽ ተማምነሽ፣‘ማን ሊነካኝ ይችላል?’ ትያለሽ።

5 በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ፣ሽብር አመጣብሻለሁ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤“እያንዳንዳችሁ ትሰደዳላችሁ፤በሽሽት ላይ ያሉትንም የሚሰበስብ አይገኝም።