13 ትንቢት እየተናገርሁ ሳለ፣ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወዮ! የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን?” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
15 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወንድሞችህ፣ የራስህ ዘመዶችና የእስራኤል ቤት ሁሉ፤ ‘ከእግዚአብሔር ርቀዋል፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለኛ ተሰጥታናለች’ ብለው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተናገሩባቸው ናቸው።
16 “ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በአሕዛብ መካከል ብሰድዳቸውም፤ በአገሮች መካከል ብበታትናቸውም፣ በሄዱባቸው አገሮች ሁሉ ለጥቂት ጊዜ መቅደስ ሆኜአቸዋለሁ’ ”።
17 “ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።”
18 “ወደዚያ በተመለሱ ጊዜ የረከሱ ምስሎቿንና ጸያፍ ተግባሯን ያስወግዳሉ።
19 የማያወላውል ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ አዲስ መንፈስ በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አወጣለሁ፤ ሥጋ ልብም እሰጣቸዋለሁ።