1 ከዚያም ያ ሰው በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጩ አደባባይ በማምጣት፣ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ትይዩና በሰሜን በኩል ባለው ግንብ ትይዩ ወደ አሉት ክፍሎች አመጣኝ።
2 በሩ በሰሜን ትይዩ የሆነው ሕንጻ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበር።
3 ከውስጠኛው አደባባይ ሃያ ክንድ ርቀት ላይና በአንጻሩም ከውጩ አደባባይ የንጣፍ ድንጋይ ፊት ለፊት ርቀት ላይ በሦስት ደርቦች ትይዩ የሆኑ ሰገነቶች ነበሩ።
4 ከክፍሎቹ ፊት ለፊት ወርዱ ዐሥር ክንድ፣ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ የሆነ መተላለፊያ በውስጥ በኩል ነበር። የክፍሎቹም በሮች በሰሜን በኩል ነበሩ።
5 የላይኞቹ ክፍሎች ጠበብ ያሉ ናቸው፤ ምክንያቱም ሰገነቶቹ ታችና መካከል ላይ ካሉት ከሕንጻው ክፍሎች ይልቅ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ይዘውባቸዋልና።
6 አደባባዮቹ ዐምዶች ሲኖሯቸው፣ በሦስተኛው ደርብ ላይ ያሉት ክፍሎች ግን ዐምድ የላቸውም። ስለዚህ የወለላቸው ስፋት በታችኛውና በመካከለኛው ደርብ ካሉት ክፍሎች ይልቅ ጠበብ ያለ ነው።