ኤርምያስ 40:7-13 NASV

7 በየሜዳው የነበሩት የጦር መኰንኖችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ እንደ ሾመውና ወደ ባቢሎን በምርኮ ባልተወሰዱት በምድሪቱ ድኾች ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠው በሰሙ ጊዜ፣

8 ወደ ምጽጳ፣ ጎዶልያስ ዘንድ መጡ፤ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያ ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፣ የተንሑት ልጅ ሠራያ፤ የነጦፋዊው የዮፌ ልጆች፣ የማዕካታዊ ልጅ ያእዛንያን ሰዎቻቸውም ነበሩ።

9 የሳፋን ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ሲል ቃል ገባላቸው፤ “ለባቢሎናውያን መገዛት አትፍሩ፤ በምድሪቱ ተቀምጣችሁ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካም ይሆንላችኋል።

10 እኔም ራሴ ወደ እኛ በሚመጡት በባቢሎናውያን ፊት ልቆምላችሁ፣ በምጽጳ እቀመጣለሁ፤ እናንተ ግን ወይን፣ የበጋ ፍሬና ዘይት አምርቱ፤ በማከማቻ ዕቃዎቻችሁ ውስጥ ክተቱ፤ በያዛችኋቸውም ከተሞች ተቀመጡ።”

11 በሞዓብ፣ በአሞን፣ በኤዶምና በሌሎች አገሮች ሁሉ የነበሩ አይሁድ በሙሉ የባቢሎን ንጉሥ፣ ሰዎችን በይሁዳ እንዳስ ቀረና የሳፋን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ፣

12 ሁላቸውም ከተበታተኑበት አገር ሁሉ ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሱ፤ በምጽጳ ወደ ሚኖረውም ወደ ጎዶልያስ መጡ፤ ወይንና የበጋ ፍሬም በብዛት አከማቹ።

13 የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ገና በየሜዳው የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው፣