7 እኔም በታዘዝሁት መሠረት አደረግሁ፤ በቀን ጓዜን ጠቅልዬ እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፤ በምሽትም ግንቡን በእጄ ነደልሁት፤ እያዩኝም በምሽት ጓዜን በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ አወጣሁ።
8 በማግስቱም ጠዋት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
9 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ የምታደርገው ምንድን ነው?’ ብለው ጠይቀውህ አልነበረምን?”
10 “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በዚያ ለሚገኙት ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው’ ”።
11 ‘እኔ ምልክታችሁ ነኝ’ በላቸው።“እኔ እንዳደረግሁት፤ እንዲሁ በእነርሱ ይደረግባቸዋል፤ በምርኮኛነትም ተሰደው ይሄዳሉ።
12 “በመካከላቸው ያለው መስፍን በምሽት ጓዙን በትከሻው ተሸክሞ ይወጣል፤ ሾልኮ እንዲሄድ ግንቡ ይነደልለታል፤ ምድሪቱንም እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።
13 መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ነገር ግን እርሷን ሳያያት በዚያ ይሞታል።