26 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም።
27 ኀጢአተኛው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ በታማኝነትና በቅንነት ቢኖር ሕይወቱን ያድናል።
28 የፈጸመውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ካደረገው ክፋት ሁሉ ስለ ተመለሰ፣ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
29 የእስራኤል ቤት ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ! መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነችውስ የእናንተ መንገድ አይደለችምን?
30 “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየ ሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
31 በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?
32 ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!