ሕዝቅኤል 20:36-42 NASV

36 በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋር እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

37 ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋር አጣብቃችኋለሁ።

38 በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

39 “ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖታቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።

40 በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋር በዚያ እሻለሁ።

41 ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበ ሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።

42 ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።