ሕዝቅኤል 26:11-17 NASV

11 መንገዶችሽ ሁሉ በፈረሶቹ ኮቴ ይረጋገጣሉ፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ታላላቅ ምሰሶዎችሽ ወደ ምድር ይወድቃሉ።

12 ሀብትሽን ይዘርፋሉ፤ ሸቀጥሽን ይበዘብዛሉ፤ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የተዋቡ ቤቶችሽን ያወድማሉ፤ ድንጋይሽን፣ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ።

13 ዘፈንሽን ጸጥ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም የበገናሽ ድምፅ አይሰማም።

14 የተራቈተ ዐለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆኛለሽ፤ እንደ ገናም ተመልሰሽ አትሠሪም እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

15 “ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላል፤ ‘የቈሰሉት ሲያቃስቱ፣ በውስጥሽም ጭፍጨፋ ሲካሄድ፣ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን?

16 የባሕር ጠረፍ መሳፍንት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ይጥላሉ፤ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውን ያወልቃሉ። ፍርሀት ተከናንበው በመሬት ላይ በመቀመጥ ባለማቋረጥ፣ እየተንቀጠቀጡ በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ይሸበራሉ፤’

17 ስለ አንቺም እንዲህ ብለው ሙሾ ያወርዳሉ፤“በባሕር ሰዎች የሚኖሩብሽ፣ባለዝናዋ ከተማ ሆይ፤ እንዴት ጠፋሽ!ከነዋሪዎችሽ ጋር፣የባሕር ላይ ኀያል ነበርሽ፤በዚያ በሚኖሩትም ሁሉ ዘንድየተፈራሽ ነበርሽ።